Categories

ጠይም ፅጌረዳ 🌹


ውበትሽን ሳይ ምናለ ሰዓሊ ሆኜ ብሆን ኖሮ እላለሁ። እንደ ሞናሊዛ ዘመን ተሻጋሪ አድርጌ ስዬሽ የውበት መለኪያ ባደርግሽ ብዬ አስባለሁ። ጠይም ቆዳሽ የውበት ባንዲራ እንዲሆን ስል ሰዓሊ ብሆን ኖሮ እላለሁ። ግን አይደለሁም። ቀለማትን ማስማማት ባልችልም ቃላትን ግን ማስማማት እችልበታለሁ። አንድ ሺህ ቃላት የአንድ ስዕልን ያህል አይናገሩም ይባላል። አንድ ሺህ አይደለም የፈጀውን ይፍጅ እኔ ግን በማውቀው በምችለው በቃላት እስልሻለሁ። የፈጀውን ይፍጅ። እስልሻለሁ።
ብዕሬን አነሳሁ፤ ቃላት ውስጥ ነከር ነከር
ሸራዬንም ወጠርኩ ፤ ውበት ለመመስከር
ሞናሊዛ የቷ? ኧረ እንጃባቷ ፤ እንዲሉ አደርጋለሁ
ቀለም ሳልበጠብጥ ቃላት እየቀባሁ ውበት እስላለሁ።

ብዕሬን አነሳሁ
ቃላት ውስጥ ነከር ነከር
መልክሽን እያየሁ
ከትውስታ ማህደር
ብዕሬን ቃላት ውስጥ ነከር ነከር


~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
በደብዛዛ ቀይ ብርሃን ታጅበን ቁጭ ብለን ቡና እየጠጣን ነው። እኔም ሶስቱን የስሜት ህዋሳቴን ላንቺ ገብሬ አጠገብሽ ቁጭ ብያለሁ። በዓይኔ እያቀፍኩ – ለጆሮዬ ምግብ የሆነውን ለስላሳ ድምፅሽን እየሰማሁ – በእጆቼ ጥጥ እጆችሽን እየዳበስኩ ትኩረቴን በሙሉ አንቺ ላይ አሳርፌ የውበትሽ ታዳሚ ሆኛለሁ። መልክሽን እያየሁ ፊትሽ ላይ የተጣበቁት ድክም ያሉ ቀይ ጨረሮች አስቀኑኝ። ጠይም መልክሽ የብርሃን ፍንጣቂዎችን ብቻ ሳይሆን የኔንም ዐይን ስቦ ያስቀራል። ልክ እንደተለከፈ ሐይቅ ስቦ አስገብቶ ከውበት ጥልቀት የሚያሰምጥ ጠይምነት። መሐል ለመሐል ተከፍሎ ልሙጥ ተደርጎ የተያዘ ጥቁር ባህር የመሰለ ፀጉርሽ ላይ አረፍኩ። አለፍ አለፍ ብለው እንደ ማዕበል ቀና ቀና ያሉትን የፀጉር ዘለላዎች በጣቶቼ ደምደም እያደረግሁ በሰበቡ እንሳፈፋለሁ። እጆቼንም ሆነ ዓይኖቼን ካንቺ ላይ ማንሳት አይቻለኝም። እጆቼን ከፀጉርሽ ቀስ እያደረግሁ አውርጄ በአንድ በኩል ስትስቂ ስርጉድ የሚለው ጉንጭሽን ስዳብሰው የተደፋ ወተት ላይ በጥንቃቄ የተቀመጡ የሚመስሉ ቡኒ ዓይኖችሽ ስብር ይላሉ። ብዙ ያዩ – ብዙ የሚያውቁ ንፁህ ዓይኖች። ስሜትሽን – እውነትሽን – ተስፋሽን አዝለው የያዙ። አእምሮሽ ከሚነግርሽ ባለፈ ጥሩውን ለማየት የሚጓጉ ብዙ ያዩ – ብዙ የሚያውቁ ንፁህ ዓይኖች። በመሐላቸው የቆመ አነስ ያለ ግን ስልክክ ያለ የአፍንጫ ድንበር ከስሩ ያለውን ምጥን ከንፈርሽን የሚጠብቅ ንቁ ወታደር ይመስላል። ከንፈርሽም ደብዛዛው ቀዩ መብራት ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ሰብሰብ ብሎ የሳመሽ የሚያስመስል ቀላ ያለ የከንፈር ቀለም ተቀብቷል። ብሳለመው የልቤን ክብደት የሚያቀልልኝ – ብስመው ፀሎቴን የሚያሰምርልኝ ምጥን ያለ የቀላ ከንፈር። ከጀርባው ያሉትን ከላይ በአግባቡ የተሰደሩ – ከስር ግን በላይ የተደራረቡ የብርሃን ብልጭታ – የደስታ ምልክት የሆኑ ጥርሶችሽን የሚጠብቁ ቀይ ማር የተቀቡ ምጥን ከንፈሮች።
እጄ ከፀጉርሽ ወደ ጉንጭሽ – ከጉንጭሽ ወደ አንገትሽ ቀስ እያለ ይወርዳል። ቀይ የብርሃን ስካርፍ የለበሰ አንገት። ውበትሽ ያሳወረኝ ይመስል የገላሽን እያንዳንዷን ሚሊሜትር በጣቶቼ እንደ ብሬል እያነበብኩ ማወቅ እፈልጋለሁ። የገላሽን አሰራር በመዳፌ እየዳበስኩ በጣቴ እያነበብኩ ወጣ ገባውን ማወቅ እፈልጋለሁ። አሁን ግን ከአንገትሽ ቀስ እያልኩ በጣቶቼ እያነበብኩ በትከሻሽ አድርጌ በክንድሽ አልፌ እንደ ስፖንጅ የሚያሰምጠው መዳፍሽ ጋር እደርሳለሁ። ለስላሳ – የሚያምሩ ጠይም እጆች። ያልበዛ ያላነሰ በልክ ያደጉ ጥፍሮች። ፈዛዛ ቀይ ብርሃን የደበቃቸው ግራጫ ቀለም የተቀቡ የሚያምሩ ጥፍሮች። ውበትን ሌላ ትርጉም የሚሰጥ ውበት። ሙሉ ገላሽ እንደ መልክሽ ሁሉ ስቦ የሚከት ነው። በሰመጥኩ – ጠፍቼ በቀረሁ ያስብለኛል። ያገኘው አካልሽ ላይ ሁሉ በስሱ የተኛው ፈዛዛው ቀይ ብርሃን አስቀናኝ።

በጨለማ ቦታ ዐይኖቹን ለሳለ
በምድረ በዳ ላይ ተስፋን ለተከለ
ብዙ ተሸፍኖ ትንሽ በታየበት ፍቅርን ለከጀለ
ፈዛዛ ብርሃን ውስጥ ደማቅ ውበት አለ
ጠይም ጽጌረዳ በቀይ ብርሃን አቅፎ በዉስጡ ያዘለ።

ጠይም ጽጌረዳ 🌹